አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢቲሃድ አየር መንገድ ከአቡ ዳቢ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ዕለታዊ በረራ በዛሬው ዕለት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢቲሃድ አየር መንገድ ጋር በአቪየሽን ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችለውን የስትራቴጂያዊ አጋርነት ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡
በሁለቱ አየር መንገዶች ስምምነት መሠረት የኢቲሃድ አየር መንገድ በዛሬው ዕለት ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ዕለታዊ በረራ ጀምሯል፡፡
በበረራ ማስጀመሪያ ሥነሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዲሁም የኢቲሃድ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አንቶናልዶ ኔቬስ ተገኝተዋል።
አቶ መስፍን ጣሰው በወቅቱ እንዳስታወሱት፤ ሁለቱ አየር መንገዶች ተባብረው ለመስራት በፈረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ወደ ስራ ገብተዋል።
የአጋርነት ስምምነቱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ አቅም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመሳሳይ የዚሁ ስምምነት አካል የሆነውን በረራ ባለፈው ሐምሌ ወር ወደተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ዛይድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ መጀመሩ ይታወቃል።
እነዚህ አዳዲስ በረራዎች በተለይም የቱሪዝምና የንግድ ዕድሎችን በማስፋት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በኃይለማርያም ተገኝ