የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ገጽታ ያደሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ…

By sosina alemayehu

October 09, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ የኢትዮጵያን ገጽታ በድጋሚ ያደሰ ትልቅ ፕሮጀክት ነው አሉ ምሁራን።

የሃይድሮ ፖለቲክስ መምህርና ተመራማሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በሐሳብ እና በሌሎች መንገዶች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ዘንድ የግድቡ ተገቢነትን በማስረዳት ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ያዕቆብ (ፕ/ር)÷ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በጋራ በመቆም ግድቡ እንዲጠቀቅ ማድረጋቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሪ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ የዓለም ሚዲያዎች አፍሪካን ብሎም ኢትዮጵያን በተመለከተ በዓለም ሕዝብ ዘንድ በመጥፎ መልኩ ገጽታዋን ቀርጸውት እንደነበር አመላክተዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ተባብረው እና በጋራ በመሆን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ገንብተው በማጠናቀቅ ቁርጠኝነታቸውንና ጀምሮ የመጨረስ አቅማቸውን በድጋሚ ለዓለም ሁሉ አሳይተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን አርበኞች በአንድነት በመቆም ያስመዘገቡት የዓድዋ ድል ሊቀለበስ የማይችል እና ማንነታችንን ያረጋገጠ ድል እንደሆነ ሁሉ፤ ሕዳሴ ግድብም ሌሎች ሀገራት በተደጋጋሚ ሲያደርጉት የነበረውን ተጽዕኖ በመቋቋም ዕውን የሆነ ድል መሆኑን አንስተዋል።

የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ የምታቀርባቸው ሐሳቦች ተቀባይነት እንዲኖራቸው እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ባለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ትልቅ ድል መሆኑንም አብራርተዋል።

በዮናስ ጌትነት