አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኒያ ፋውንዴሽን የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ኦቲዝምና ተያያዥ የዕድገት እክል ያለባቸውን ሰዎች ማህበራዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራሁ ነው አለ፡፡
ማዕከሉ በደብረ ብርሃን ከተማ የኦቲዝምን ምንነት በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በዚሁ ወቅት፥ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ከማህበራዊ ተሳትፎ የተገለሉ የዕድገት እክል ያለባቸው ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ኒያ ፋውንዴሽን ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፥ በዚህ ረገድ የሚከናወነው ስራ ውጤታማ እንዲሆን ከተማ አስተዳዳሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ኒያ ፋውንዴሽን በወ/ሮ ዘሚ የኑስ የተመሰረተ ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፥ ላለፉት 23 ዓመታት ኦቲዝምና ተያያዥ የዕድገት እክል ለገጠማቸው ሰዎች ሁለንተናዊ የተሃድሶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ተመላክቷል።
የማዕከሉ የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ክብረአብ ጴጥሮስ እንዳሉት፥ ፋውንዴሽኑ ኦቲዝምና ተያያዥ የዕድገት እክል ለገጠማቸው ሰዎች ሁለንተናዊ የተሃድሶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ከጊዳቦ ፖሊሲ ማዕከል ጋር በመተባበር ለኦቲዝም የተጋለጡ ልጆችን የሚያሳድጉ እናቶችን በገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሰማሩ እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑንም ነው አስተባባሪው የገለጹት፡፡
በሰላም አሰፋ