አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኮሜሳ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፍ በትኩረት እሰራች እንደምተገኝ ማስገንዘብ ተችሏል አሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሳተፉበት 24ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የመሪዎች ጉባኤ ትናንት በኬንያ ናይሮቢ ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ዲጂታላይዜሽን የኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን አንስተዋል።
የኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭን ጨምሮ ጠንካራ የዲጂታል መሠረተ ልማት በመገንባትና ሰፊ ክህሎት ከማፍራት አኳያ ኢትዮጵያ አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበች ነው ማለታቸውንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች የኢትዮጵያን ዕድገትና ለውጥ ለመምራት ብሎም ጠንካራ ዲጂታል መሠረት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓትና የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታል የማድረግ ተግባራት ለዘርፉ እድገት ቁልፍ ምሳሌ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የዲጂታላይዜሽን ጥረቶች ከፍተኛ ውጤት እንዲያስገኙ ከቀጣናዊ ግቦች ጋር ማጣጣም እንደሚገባም በመድረኩ ላይ አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ወጣቶች ለአህጉሪቱ ልማትና ዕድገት ወሳኝ በመሆናቸው የአህጉሪቱን የጎለበተ የወጣቶች ተሰጥኦና አቅም መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡