አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተጻፈው ‘የመደመር ትውልድ’ መጽሐፍ በፓኪስታኑ ኡርዱ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ ቀርቧል።
ይህ የትርጉም ሥራ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) እና በፓኪስታን የባህልና ቅርስ ሚኒስትር አውራንግዜብ ካን ኺቺ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመጽሐፉን የትርጉም ስራ የፓኪስታን ብሔራዊ ቋንቋ ማስተዋወቂያ መምሪያ በተሳካ ሁኔታ አስፈጽሞታል ነው የተባለው።
በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)÷ የመጽሐፉ በኡርዱ ቋንቋ መዘጋጀት በፓኪስታን በሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራን እና ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈውን የመደመር ፍልስፍና በጥልቀት እንዲረዱ ትልቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የኡርዱኛ ተናጋሪዎች የመጽሐፉን ዋና መልዕክት በቀላሉ እንዲረዱ ብሎም ኢትዮጵያ የምትከተለውን የጋራ ብልጽግና አስተሳሰብ ለማስተዋወቅ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
መጽሐፉ በፓኪስታን ዩኒቨርሲቲዎች፣ ቤተ መጽሐፍት እና የምርምር ተቋማት እንደሚሰራጭ ተገልጿል፡፡
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የእውቀትና የልምድ ልውውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡
የመጽሐፉ መተርጐም በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል የተመሰረተው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውጤት ሲሆን ለቀጣይ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርም መሰረት የሚጥል እንደሆነ ተመላክቷል፡፡