አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝቡን አዳጊ ፍላጎቶች ለማሟላት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ጊዜ የማይሰጥ የቤት ስራ ነው አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
ሀገራዊ የተጣጣመ የታክስ ስርዓት በመፍጠር ታክስ ፍትሀዊነትና ሀገራዊ እድገት ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ የባለድርሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሀገራዊ ሪፎርሞች በውጤታማነት መተግበራቸው በቴክኖሎጂ የዘመነ ቀልጣፋ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት እንዲዘረጋ መሰረት ጥሏል።
በለውጡ የተገኙ የልማት ትሩፋቶች የፈጠሩት መተማመን፣ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡ እንዲሁም የአመራር ክትትልና ድጋፍ መጠናከሩና የዜጎችን ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎች መከናወናቸው ገቢ እንዲያድግ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ነው ያሉት፡፡
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በየደረጃው ገቢ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፥ ታማኝ ግብር ከፋዮች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሀገር የገቢ ዘርፍ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርምን በተናበበ አግባብ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በተለይም የታክስ ስወራና የግብር ማጭበርበርን የመሳሰሉ ህገ ወጥ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ ቢሆንም በዘላቂነት ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለዚህም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የተቋም ግንባታ ስራዎችን ማጠናከር፣ የታክስ የመክፈል ባህልን ለማዳበር በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የሕዝቡን አዳጊ ፍላጎቶች ለመመለስ እንዲቻል ባለው እምቅ የገቢ አቅም ልክ ገቢን በስርዓት መሰብሰብ ጊዜ የማይሰጥ የቤት ስራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡