አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪስት መዳረሻዎችን ይበልጥ ለማስፋፋት በትብብር መስራት ይገባል አሉ ከፍተኛ የቱሪዝም ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ፡፡
ከፍተኛ የቱሪዝም ባለሙያው ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ የባሕር በር ለጎብኚዎች አንዱ መዳረሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጎብኚዎች ለመዋኘት፣ በጀልባዎች ለመንሸራሸር፣ በባሕር ውስጥ የሚገኙ እንደ ዓሣ ነባሪ ያሉ እንስሳትን ለማየት፣ እንዲሁም በሌሎች አማራጮች በውሃ ላይ ለመዝናናት ይፈልጋሉ፡፡
ለዚህም ባሕር በር ለቱሪዝሙ ዘርፍ አንዱ መሰረት መሆኑን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያ ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያጣችው የባሕር በር በቱሪዝም ብሎም በሌሎች ዘርፎች እድገት ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እምቅ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዳሏት አውስተዋል፡፡
የአየር ንብረት፣ የቦታ አቀማመጥ፣ የውሃ አካላትና ሌሎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ስጦታዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ በሌሎች ሀገራት የማይገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ መሆኗንም አመልክተዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባህላዊ ክዋኔዎች፣ የአኗኗር ዘዬ፣ አመጋገብ፣ አለባበስ እና በርካታ መገለጫዎች የጎብኚዎችን ቀልብ እንደሚስቡም አስገንዝበዋል፡፡
በብርሃኑ አበራ
ከፍተኛ የቱሪዝም ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ ፡-https://www.youtube.com/watch?v=0HZo62EXPnU