የሀገር ውስጥ ዜና

ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሠንደቅ ዓላማ ቀን አከበረ

By sosina alemayehu

October 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት 18ኛውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች አክብሯል።

ቀኑ ‘ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ’ በሚል መሪ ሀሳብ የአገልግሎቱ አመራሮች እና አባላት በተገኙበት ተከብሯል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ሀገርን ከወራሪዎች ለመከላከልና ነጻነትን ለማስጠበቅ የተደረገው ተጋድሎ ምልክት ነው ብለዋል።

የአገልግሎቱ አባላትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነት እና ክብር ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ስምሪት የሠንደቅ ዓላማውን አደራ በልባቸው በመያዝ እስከ መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ይከፍላሉ ነው ያሉት።

ሠንደቅ ዓላማው መላው ኢትዮጵያውያንን ለጋራ ዓላማ የሚያሰባስብ የማንነት መገለጫ ዓርማ መሆኑን ገልጸው፤ የአገልግሎቱ አባላት በሠንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ሀገራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮን በላቀ መንፈስ እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውን አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል።