የሀገር ውስጥ ዜና

የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የሠንደቅ ዓላማችን ከፍታ የሚጨምሩ ናቸው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Yonas Getnet

October 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጠናቀቁና የተጀመሩ ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ስብራቶቻችንን የሚጠግኑና የሠንደቅ ዓላማችን ከፍታ የሚጨምሩ ናቸው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

18ኛው ብሄራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች የሠንደቅ ዓላማችን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ናቸው።

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅና የዘመናት የኢኮኖሚ ስብራትን መጠገን የሚያስችሉት የጋዝ ማውጣትና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ሥራ መጀመርም የሠንደቅ ዓላማችን ከፍታ ይጨምራል ነው ያሉት፡፡

የአገልግሎቱ አመራሮችና ባለሙያዎች ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን በማሳካት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው ÷ ሠንደቅ ዓላማችን የሀገርና የሕዝብ የክብር ምልክት መሆኑን በመረዳት የሠንደቃችን ክብር ከፍ በሚያደርጉ ሀገራዊ ውጥኖች ላይ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡