የሀገር ውስጥ ዜና

የአርሶ አደሩን አኗኗር ለማሻሻል ያለመው የገጠር ኮሪደር ልማት…

By Adimasu Aragawu

October 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር የአርሶ አደሩን አኗኗር ለማሻሻል ያለመውን የገጠር ኮሪደር ልማት ለማስፋፋት በትኩረት ይሰራል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በክልሉ ሀላባ፣ ከምባታ፣ ሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የገጠር ኮሪደር ልማት አካል ሆነው የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮች ርክክብ ሥነ ሥርዓት በቅርቡ አካሂደዋል።

በመንደሮቹ የተገነቡ መኖሪያዎች መኝታ ቤት፣ ምግብ ለማብሰል የሚያገለግል የባዮጋዝ መሣሪያ፣ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ እንዲሁም ለእንስሳት እርባታ የተለየ ስፍራ ተሟልቶላቸዋል።

ይህንን ሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታ በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋፋት አቅጣጫ ተቀምጦ በቀጣይነት እንደሚሰራ አቶ ኡስማን ሱሩር ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ሞዴል የገጠር መንደሮቹ ተመጣጣኝ ወጪ የሚጠይቁና በአካባቢው ከሚገኙ ግብዓቶች የተገነቡ እንዲሁም አርሶ አደሩ ጤናማ እና ክብር ያለውን ህይወት እንዲኖር የሚያስችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

በክልሉ የተከናወነው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ስነ ምህዳራዊ ፋይዳን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህም ዘላቂ ልማት፣ የኢኮኖሚ እድገት እና የተረጋጋ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት አንስተው÷ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ለሌሎች አካባቢዎች ሞዴል በሚሆንበት መንገድ በፍጥነት እና በጥራት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነው የገጠሩ አካባቢ ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን አስታውሰው÷ የኮሪደር ልማቱ በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ አኗኗርን እንደሚፈጥር እና የአርሶ አደሩን ህይወት እንደሚቀይር አመላክተዋል።

የኮሪደር ልማቱ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ከተማ የሚሄደውን አርሶ አደር በሚኖርበት ተረጋግቶ እሴት ጭመራ ላይ እየሰራ እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል።

የገጠር ኮሪደር አጠቃላይ የሕብረተሰብ ሽግግር የሚያመጣ እና መሰረተ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች መያዙን ጠቅሰው÷ ልማቱን ሕብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ማከናወኑን ተናግረዋል።

ለገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!