አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ባንክ የቀጣናው ግቦች ያለ ኢትዮጵያ አጋርነት ሊሳኩ አይችሉም አሉ የባንኩ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ም/ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ፡፡
ንዲያሜ ዲዮፕ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የምታከናውናቸው ፕሮጀክቶች ውጤታማነት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን እንዳደረጉ ገልጸው ÷ በቆይታቸውም ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ነው ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ቁልፋ ስትራቴጂያዊ አጋር ናት ያሉት ም/ፕሬዚዳንቱ ÷ የባንኩ የቀጣናው ግቦች ያለ ኢትዮጵያ አጋርነት ሊሳኩ እንደማይችሉ አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የታለመለትን ግብ እንዲመታ የዓለም ባንክ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በግብርና፣ በሎጂስቲክስና እና ሌሎች ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ