የሀገር ውስጥ ዜና

የገንዘብ ፖሊሲው ጠንካራ እና ሰፋ ያለ እድገትን እየደገፈ ነው – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

By Abiy Getahun

October 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የገንዘብ ፖሊሲው በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመራ ጠንካራ እና ሰፋ ያለ እድገትን እየደገፈ ነው አሉ።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን ከጉባኤው ተሳታፊ የአውሮፓ፣ አሜሪካ እና አፍሪካ ባለሀብቶች ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

ስታንዳርድ ባንክ ግሩፕ የተሰኘው ተቋም ባዘጋጀው በዚህ የውይይት መድረክ በአፍሪካ ኢኮኖሚ እና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ የሀሳብ ልውውጥ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ የሪፎርም ስራዎች፣ የዕድገት ሁኔታ እና እምቅ የኢንቨስትመንት እድሎችን በተመለከተ ለመድረኩ ሰፊ ማብራሪያ ያቀረቡት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ ባለሃብቶቹ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ በተመለከተ ላነሱት ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስቀጠል፣ የፋይናንሺያል ሴክተሩን ለማዘመን እና የባለሃብቶችን እምነት ለማሳደግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የፋይናንስ አካታችነትን ለማስፋፋት እና በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን ለማራመድ ያለመ የሪፎርም ስራ ተግባራዊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራና የተስተካከለ የሂሳብ አያያዝን በመጠበቅ እና ቀስ በቀስ የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ ላይ ያተኮረ፣ ጠንካራ እና ሰፋ ያለ እድገትን እየደገፈ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዘንድሮው የዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ የፖሊሲ ግልፅነትን ለመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያን ተወዳዳሪና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!