አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጀመሩት የአዳራሽ እና አካባቢን የማስዋብ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ ለጋሾች የእራት ግብዣ አድርገዋል።
አዲሱን የኋይት ሀውስ ታላቅ አዳራሽ እና አካባቢን የማስዋብ የ200 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት የሚደግፉ ለጋሾችን እና ባለሃብቶችን በነጩ ቤተ መንግስት እራት ጋብዘዋል።
ባለፈው መስከረም ወር ግንባታ የጀመረው እና 90 ሺህ ስኩዌር ጫማ የሚሸፍነው አዳራሽ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን ያስተናግዳል።
እንደ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ አሜሪካን በዓለም መድረክ በተሻለ ሁኔታ እንዲወክል የሚያስችል ነው።
አሁን ላይ ያለው መሠረተ ልማት መሪዎችን ለመቀበል እና ለማነጋገር ብሎም የተለያዩ ሁነቶችን ለማስተናገድ ምቹ አለመሆኑንም አንስተዋል።
የታላቁ አዳራሽ ፕሮጀክት ከኋይት ሀውስ ንድፍ ጋር የሚስማማ ተደርጎ እንደሚገነባ ገልጸው፤ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ ባለሃብቶችን እና ኩባንያዎች አመስግነዋል።
በእራት ግብዣው ላይ የማይክሮሶፍት፣ የሜታ፣ የጉግል፣ የአማዞን እና የቲ-ሞባይል ተወካዮችን ጨምሮ በርካታ የክሪፕቶ ስራ ፈጣሪዎች እና ባለሃብቶች ተገኝተዋል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዛሬ ላይ የጀመሩት ‘የሌጋሲ ዲነር’ ስራ ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በሚል መጀመሩ ይታወቃል።
ዜጎች እና ባለሀብቶች የነቃ ተስትፎ ባደረጉበት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ ውጪ በሶስት ቦታዎች ማለትም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮይሻ፣ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ወንጪን ማልማት መቻሉ ይታወቃል።
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!