ስፓርት

በ25 ዓመቱ 27 ሀትሪክ የሰራው ሃላንድ…

By Adimasu Aragawu

October 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ25 ዓመቱ 27 ሀትሪክ የሰራው የማንቼስተር ሲቲው የፊት መስመር ተጫዋች ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ፡፡

የሲቲው የፊት መስመር ተጫዋች ሃላንድ አሁን ላይ በአጠቃላይ በእግር ኳስ ሕይወቱ ከዕድሜው ቁጥር በላይ ሀትሪክ በመስራት የራሱን ደማቅ ታሪክ እየጻፈ ይገኛል፡፡

በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የፊት መስመር ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ሃላንድ ፍጥነቱ፣ ጥንካሬው፣ ቦታ አያያዙ እና ጎሎችን የሚያስቆጥርበት መንገድ የእሱ መገለጫዎች ናቸው፡፡

ሃላንድ በእግር ኳስ ሕይወቱ ለብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው 46 ጨዋታዎች 51 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፥ እዚህ ቁጥር ላይ ለመድረስ ትንሽ ጨዋታ የፈጀበት ተጫዋችም ሆኗል፡፡

በፈረንጆቹ 2019 ለኖርዌይ ዋናው ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን በ18 ዓመቱ ያደረገው ሃላንድ አሁን ላይ የብሔራዊ ቡድኑ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃን እየመራ ይገኛል፡፡

ሃላንድ ለክለቡም ሆነ ለሀገሩ ጨዋታዎችን ባደረገ ቁጥር በርካታ ክብረ ወሰኖችን እያሻሻለ የሚገኝ ተጫዋች ነው፡፡

ተጫዋቹ በዚህ የውድድር ዓመት ለሀገሩ እና ለክለቡ ባደረጋቸው አጠቃላይ 12 ጨዋታዎች 21 ጎሎች አስቆጥሯል፡፡

ከጀርመኑ ክለብ ቦርሲያ ዶርትሙንድ ወደ ማንቼስተር ሲቲ ከመጣ ጀምሮ በርካታ የቡድን እና የግል ስኬቶችን ማሳካት ችሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2022 ማንቼስተር ሲቲን የተቀላቀለው ሃላንድ በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ የሶስትዮሽ ክብርን መጎናጸፉ አይዘነጋም፡፡

ማንቼስተር ሲቲ ለዓመታት ሲመኘው የነበረውን የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ሃላንድን ካስፈረመ በኋላ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሳካቱ ይታወሳል፡፡

ሃላንድ ማንቼስተር ሲቲን ከተቀላቀለ ወዲህ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

በሲቲ ቤት በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ከቡድን ስኬቱ በተጨማሪ በሊጉ ባደረጋቸው 35 ጨዋታዎች 36 ጎሎችን በማስቆጠር በአንድ የውድድር ዓመት ብዙ ጎል በሊጉ በማስቆጠር ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ አይዘነጋም፡፡

በሊጉ ለተከታታይ ሁለት የውድድር ዓመት የሊጉ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ በመጨረስ የወርቅ ጫማውን ሁለት ጊዜ በተከታታይ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ሃላንድ በአንድ የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊግ ወጣት ተጫዋች እና የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ያሸነፈ ብቸኛው ተጫዋች ነው።

ሃላንድ ለማንቼስተር ሲቲ በሁሉም ውድድሮች 136 ጎሎችን በማስቆጠር ከምንጊዜም የማንቼስተር ሲቲ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች አንዱ በመሆን 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ በዚህ የውድድር ዓመት በሊጉ ለማንቼስተር ሲቲ ባደረጋቸው 7 ጨዋታዎች 9 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉን ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት በመምራት ላይ ነው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ