አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚምዲዚ የኢትዮጵያ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደነቅ ቁርጠኝነት አሳይቷል አሉ።
በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት ተወካይዋ፤ ይህንን የኢትዮጵያ ጥረት የዓለም ምግብ ድርጅት እየደገፈ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ አይነት ተያያዥ የአየር ንብረት ለውጥ መርሐ ግብሮችን እየተገበረ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚህም ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በግብርና መር የምግብ ስርዓቱ ውስጥ ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ኢንቨሰት እንዲያደርጉ የሚያስችል ውይይት ከኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ አመራሮች ጋር በማድረግ ለላቀ ውጤት በመሰራት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ ሀገር ናት ያሉት ተወካይዋ÷ ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም በርካታ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን የውጭ ኢንቨስትመንት የበለጠ ምቹ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ፋኦ በኢትዮጵያ የግብርና መር የምግብ ስርዓት ውስጥ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ