የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል በመደመር እሳቤ የትምህርት ዘርፉን ስብራት ለመጠገን የተከናወኑ ሥራዎች…

By Melaku Gedif

October 17, 2025

‎አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በመደመር እሳቤ ኢኒሼቲቮች የትምህርት ዘርፉን ሥብራት ለመጠገን በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል አሉ በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሳዳት ነሻ።

የ2018 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ጉባዔ”ትምህርት ለሰው ሃብት ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው፡፡

አቶ ሳዳት ነሻ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የመደመር እሳቤ ውጤት የሆኑ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር የትምህርት ዘርፉን ስብራት ለመጠገን በተሰሩ ሥራዎች የሚለኩ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

የሰለጠኑና የበለጸጉ ሀገራት ካሉበት ምዕራፍ የደረሱት እውቀት እና ቴክኖሎጂ ላይ በትኩረት በመስራታቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሃሳብ፣ በአመለካከት፣ በተግባር እንዲሁም በቴክኖሎጂ የበቃ ትውልድ ለመፍጠር ትምህርት ጉልህ ሚና እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በክልሉ የትምህርት ዘርፉን የቆየ ሥብራት ለመፍታት የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ከ18 ሺህ በላይ የቅድመ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች በሕብረተሰብ ተሳትፎ መገንባታቸውን ጠቁመው ÷ በምገባ መርሐ ግብርም መጠነ ማቋረጥን መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የማሕበረሰቡን ችግር መፍታት የሚችል ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ጉባዔው ተሳታፊዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው÷ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሒደት የጀርባ አጥንት የሆኑት መምህራንን ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡

በመራኦል ከድር