የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ምርጫ እየሆነ የመጣው ወንጪ

By Melaku Gedif

October 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው ወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ሎጅ የተፈጥሮ ድንቅ ውበት በሚገርም ሁኔታ የተገለጠበት ሥፍራ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ፥ ወንጪ ተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና ባህል በአንድ ተሰናስለው የሚገኙበት ድንቅ የቱሪስት መዳረሻ ነው ይላሉ፡፡

የአካባቢውን መልክዓ ምድር፣ የአኗኗር ዘዬ፣ ባህል እና ማንነት በማስተሳሰር ለሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ መገንባቱን አውስተዋል፡፡

ማራኪ ተፈጥሮ የሚስተዋልበትን ወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ሎጅ የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ በትኩረት መሰራቱን አቶ ነጋ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በተለይም ለቱሪስቶች አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት አንጻር በትብብር የተከናወነው ሥራ ውጤታማ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በቱሪስት መዳረሻው የትራንስፖርት፣ የማረፊያ ክፍሎች እና ሌሎች አገልግሎቶች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡

በመንደሩ የልማት ተነሺዎች ለመቋቋሚያ የተሰሩላቸውን ደረጃቸውን የጠበቁ ቪላ ቤቶች ለጎብኚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያከራዩ ገቢ ያገኛሉ ነው ያሉት፡፡

ይህም የቱሪስቶችን ቆይታ ከማራዘም ባለፈ ጎብኚዎች አካባቢውን በደንብ ተመልክተው አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የአካባቢውን ባህላዊ ምግቦች፣ ማር፣ የቡና አፈላል ሥርዓት እና ሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎችን ለጎብኚዎች በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደርን እየጎበኙ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡

የቱሪስት ፍሰቱ ይበልጥ እንዲጨምርም አካባቢውን የማስተዋወቅ ሥራ ላይ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደርን በመጎብኘት አይረሴ ጊዜ እንዲያሳልፉም ጥሪ አቅርበዋል።

በመላኩ ገድፍ