የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መረቁ

By Adimasu Aragawu

October 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ማለዳ በባሌ ዞን፣ ደሎ መና ወረዳ በመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አማካኝነት የተጀመረውን የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መርቀዋል።

ፕሮጀክቱ የወልመል ወንዝን በመስኖ በሚገባ በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን በማላቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው በሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ዘላቂ የገጸምድር የመስኖ ሥርዓት በመገንባት የግብርና ስራው ለዘመናት በዝናብ ውሃ ላይ ተመስርቶ የነበረውን የአካባቢውን ሕዝብ ዘላቂ የኑሮ ዘዴ ለማጎናፀፍ ታልሞ ተከናውኗልም ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር በሚገባበት ወቅት 20 ሺህ ለሚሆኑ አርሶአደሮች ለሚያገለግል 9 ሺህ 687 ነጥብ 45 ሄክታር የእርሻ መሬት አስተማማኝ የመስኖ አቅርቦት ይኖረዋል ብለዋል።

ይህም የግብርና ምርታማነትን የሚያሳደግ፣ ለድርቅ የማይበገር ከባቢን የሚፈጥር ብሎም በማኅበረሰቡ አዳዲስ የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመላተዋል።

ከነዚህ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ባሻገር የአካባቢውን የውሃ አስተዳደር ተቋማትን በማጠናከር፣ የአካባቢውን ሕዝብ ባለቤትነት በማሳደግ ብሎም የወልወልን ወንዝ ዘላቂ አጠቃቀም በማጎልበት የተሻለ የምግብ ሉዓላዊነት ጠቀሜታ ያገለግላል ብለዋል።