ፋና ስብስብ

የምልክት ቋንቋን ለማስፋፋት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

By Abiy Getahun

October 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን ለማልማትና ለማስፋፋት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።

ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት ‘ያለ ምልክት ቋንቋ ዕውቅና የመስማት የተሳናቸው ሰብዓዊ መብቶች ሊከበሩ አይችሉም’ በሚል መሪ ሀሳብ በዓለም ለ67ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ በእግር ጉዞ እና በሌሎች ሁነቶች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ተክላይ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የምልክት ቋንቋ ህጋዊ ዕውቅና እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

መስማት የተሳናቸው ዜጎች በማሕበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከሌሎች ማሕበረሰቦች ጋር እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው የምልክት ቋንቋ በተገቢው ልክ መበልጸግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ቋንቋው በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ተካቶ ስራ ላይ መዋል እንዳለበት ጠቁመው፤ መስማት የተሳናቸው ወገኖች የመማር፣ የመስራት እና በማሕበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

ለዚህም የምልክት ቋንቋ እንዲስፋፋ መንግስትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት እንዲሰሩበት ጥሪ አቅርበዋል።

በመስማት የተሳናቸው ማህበረሰብ እና በምልክት ቋንቋ ላይ የሚንጸባረቀው የተሳሳተ አመለካከት እንዲቀየር የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሳምንቱ በእግር ጉዞና ለመጀመሪያ ጊዜ በማርች ባንድ ታጅቦ እንዲካሄድ ከኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማሕበር ጋር በጋራ በመስራት ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት የድርሻውን ተወጥቷል።

በናትናኤል ሽፈራው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!