የሀገር ውስጥ ዜና

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አባት ነበሩ – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

By Mikias Ayele

October 20, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አባት ነበሩ አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፡፡

ለተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስከሬን በሚሊኒዬም አዳራሽ የዱዓ እና ሽኝት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ ኢትዮጵያ እጅግ ታላቅ ሰው ማጣቷንና መላው ኢትዮጵያውያን በመሪር ሐዘን ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በህይዎት ዘመናቸው ማስተዋልና እና ትዕግስትን ካስማቸው እና ድንኳናቸው አድርገው የኖሩ እንቁ ኢትዮጵያ አባትና  መልካም እውቀታቸውን ያስተማሩ በጎ መምህር እንደነበሩ አንስተዋል።

ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ አባት እንደነበሩ ያወሱት  ፕሬዚዳንት ታዬ÷ በእውቀታቸው፣ ጥበባቸው እና እርጋታቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ማሰላሰልን፣ ደግነትን ከክፋት መለየትን እየኖሩት ሲያስተምሩ ነበር ብለዋል፡፡

በህልፈታቸው መልካምነታቸውን እና ፀጋቸውን አጥተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ በልግስናቸው፣ በበጎ ስራቸው እና መልካም አበርክቷቸው በሁሉም ዘንድ ሲዘከሩ እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ መገለጫዎች የነበሩት አስተዋይነት፣ አስታራቂነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ርሕራሄ እና መልካምነት የሚፀናው ሁላችንም የእርሳቸውን መንገድ ስንከትል ነው ብለዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ