አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌማት ትሩፋት አማካኝነት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያከናወነቻቸው ተግባራት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ ይሆናል አለ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ)።
የግብርና ሚኒስቴር ከፋኦ ጋር በመተባበር “እጅ ለእጅ ለተሻለ ስርዓተ ምግብ ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም የምግብ ቀንን አክብሯል።
የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ስትተገብረው የቆየችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዘላቂነት ያለው የደን ልማት እንዲኖርና የምግብ ፍላጎቷን ለማሟላት አስችሏታል፡፡
መርሐ ግብሩ ዓለምን እየፈተነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚ ሙድዚ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራና በሌማት ትሩፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሰራችው ስራ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የዓለምን ህዝብ እየፈተኑ ካሉ ችግሮች አንዱ የምግብ እጥረት መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት በግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ያለው ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም በሚል ዘርፍ ከቀናት በፊት እውቅና መስጠቱ ይታወሳል።
በሐመልማል ዋለ