የሀገር ውስጥ ዜና

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከእስራኤል አቻቸው ጋር ተወያዩ

By Hailemaryam Tegegn

October 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከእስራኤል አቻቸው ቤዛሌል ስሞትሪች ጋር የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት የሀገራቱን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እያደገ በመጣው የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሀገራዊ የትብብር መስኮችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

ቤዛሌል ስሞትሪች በበኩላቸው፥ እስራኤል የኢንቨስትመንት ትስስሮችን በማሳደግና በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በዲጂታል ፋይናንስ፣ በውሃ ሃብት አስተዳደር፣ በመስኖና በግብርና ዘመናዊ አሰራር ዕውቀትን በማካፈል ትብብሯን ለማስፋት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ሁለቱም ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ እና እስራኤል ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር የኢኮኖሚና የልማት ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡