የሀገር ውስጥ ዜና

የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይዘቶች ይፋ ሆኑ

By Melaku Gedif

October 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የ2018 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይዘቶችን ይፋ አድርጓል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ተፈታኞች ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ አለባቸው፡፡

ተማሪዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦች፣ መምህራንና የትምህርት አመራር ለፈተና ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ፈተና የሚሸፍናቸውን የይዘት አካባቢዎች ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ለፈተና ዝግጅት የሚደረግባቸውን የትምህርት ዓይነቶችን በተመለከተ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ እስኮላስቲክ አፕቲትዩድ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ እና ባዮሎጂ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ደግሞ እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ እስኮላስቲክ አፕቲትዩድ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ እና ኢኮኖሚክስ ናቸው ብለዋል፡፡

ፈተናው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደረጃዎችን እና በተማሪው መጽሐፍ ላይ ያሉትን ሁሉንም ምዕራፎች ይሸፍናል ነው ያሉት፡፡

ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ሁሉም የትምህርት ዓይነት ፈተና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

የ9ኛ ክፍል ደግሞ የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ፈተናዎች ከቀድሞውና ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርቶች የጋራ ይዘቶችን ብቻ አካቶ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ፈተናው ማንኛውም ተፈታኝ ተማሪ ከተማረው ሥርዓተ ትምህርት እና ከተማሪው መጽሐፍ ላይ ብቻ ተመስርቶ እየተዘጋጀ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የፈተናው አስተዳደር በበይነ መረብና በወረቀት ጎን ለጎን እንደሚሰጥ ጠቁመው ÷ አብዛኛው ተፈታኝ በበይነ መረብ እንዲፈተን እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ስለሆነም ተፈታኞች ፈተናውን በበይነ መረብ ለመፈተን እራሳቸውን ከወዲሁ ሊያዘጋጁ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ