አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ቆይታችን የልማት አጋርነትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ውጤት አግኝተናል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ።
ሚኒስትሩ በዓመታዊ ስብሰባው የኢትዮጵያ ልዑክ የነበረውን ቆይታ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ልዑኩ ስኬታማ ተሣትፎ በማድረግ ስራውን አጠናቅቋል ብለዋል።
በስብሰባው የኢትዮጵያን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የሚያጠናክሩ ድጋፎች እንዲቀጥሉ ለማስቻል በአይኤምኤፍ በኩል ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር የተቻለበት ውጤታማ ውይይት አድርገናል ነው ያሉት።
በውይይቶቹ ከአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና ሌሎች ኃላፊዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ለኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።
ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ጋር በተደረገ ውይይትም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ እና የልማት ፋይናንስ ድጋፎች ተጠናክረው በሚቀጥሉባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት መደረጉን አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በተደረገ ሰፊ ውይይት የልማት አጋሮች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም እና ዕድገት እንዲያግዙ ጥሩ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
እንዲሁም ለአዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፋይናንስ በሚደረግበት ሁኔታ ዙሪያ የተለያዩ ተቋማትን የማግባባት እና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በተሳካ ሁኔታ ተሰርቷል ነው ያሉት።
የጂ20 የጋራ ማዕቀፍ የብድር ሽግሽግ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና ከአብዛኞች ሀገራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገበችው ውጤት እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ በተለያዩ መድረኮች በምሳሌነት በመቅረብ ውጤታማ ስራዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ማያገኘታቸው ታይቷል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ የልማት አጋርነትን በማጠናከር እና የሪፎም ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ድጋፍ የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የልማት ስራዎቹ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙበት ነው ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!