አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ ያላትን ሀብት ተጠቅማ ከፈጣንና ተለዋዋጩ ዓለም ጋር አብራ እንድትጓዝ በተባበረ ክንድ መስራት ያስፈልጋል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
በአፍሪካ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገው 11ኛው የጣና ፎረም በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስን (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ ምሁራንና የዘርፉ ተመራማሪዎች ተገኝተዋል።
አቶ አረጋ ከበደ በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የጣና ፎረም ከሁነት የተሻገረ አስተሳሳሪና የግንኙነት መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።
ጣና ፎረም ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሥርዓት ላይ ሆነን የምናስተናግደው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ አፍሪካ የጉዳዩ ተሳታፊና እጣፈንታዋን የምትወስንበት ለማድረግ ይረዳናል ብለዋል።
አፍሪካ በርካታ ወጣትና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት በመሆኑ ያንን ተጠቅማ ከፈጣኑና ተለዋዋጩ ዓለም ጋር አብራ እንድትጓዝ ለማስቻል በተባበረ ክንድ መስራት አለብንም ነው ያሉት።
ፎረሙ “አፍሪካ በተለዋዋጩ ሉላዊ ሥርዓት” በሚል መሪ ሐሳብ በሦስት መድረኮች ይካሄዳል።
በዓለምሰገድ አሳዬ