የሀገር ውስጥ ዜና

ልዩ የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ንቅናቄ ተጀመረ

By Hailemaryam Tegegn

October 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ለሦስት ቀናት የሚቆይ ልዩ የምዝገባ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት ጀምሯል፡፡

በተቋሙ የምዝገባ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሄኖክ ጥላሁን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ ዛሬ የተጀመረው ልዩ ምዝገባ ተመዝጋቢዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ለማምጣት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

ልዩ የምዝገባ ንቅናቄው እስከ መጪው እሁድ የሚቀጥል ሲሆን፥ በዋናነትም በትምህርት ዘርፉ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችንና በጠቅላላው የትምህርቱን ማኅበረሰብ በልዩ ምዝገባው በስፋት ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር በስፋት እየተሳሰረ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

በተለይም በስራ ቀናት ለብሔራዊ መታወቂያ መመዝገብ ያልቻሉ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ የምዝገባ አገልግሎቱ በቀጣዮቹ ሁለት የእረፍት ቀናት በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የምዝገባ አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ በመደበኛነት ከሚሰጥባቸው የኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ፖስታ ማዕከላት በተጨማሪ በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ጭምር እንደሚሰጥም ነው የገለጹት፡፡

እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ26 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፥ በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻ 40 ሚሊየን ዜጎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በተለይም የትምህርቱ ማኅበረሰብ ነገ እና ከነገ በስቲያ ቀጥሎ በሚካሄደው ልዩ ምዝገባ አማካኝነት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑና መምህራንና የትምህርት ቤቶች አመራሮች ተማሪዎችን እንዲያስተባብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡