የሀገር ውስጥ ዜና

በጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ፕሮጀክት ማሕበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

By Yonas Getnet

October 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ማሕበረሰቡን ከፕሮጀክቱ ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል አሉ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል።

‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።

ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በውይይቱ ወቅት፤ በጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ውስጥ የማያቸው ነገሮች የመጀመሪያው መሪነት ያለንን አውቀን ጸጋችንን ለይተን ጥቅም ላይ ማዋልን እንደሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ፓርኩ ተፈጥሮ ያደለው እንደሆነ እና ይህን አካባቢ ወደ ሀብትነት መቀየር እንዳልቻለ ጠቅሰው፤ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችም ያልተሟሉለት እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሄንን ዕምቅ ሀብት ለማልማት በመጀመሪያዎቹ የለውጥ ዓመታት የቅድሚያ ቅድሚያ ዕድል ካገኙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን አልምቶ አካባቢውንም በተሻለ መሰረተ ልማት ትስስር ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እና አካባቢው በዘላቂነት ሀብት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በአካባቢው በተከናወኑ የልማት ስራዎች ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን እና ማሕበረሰቡን ከፕሮጀክቱ ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የቱሪዝም ዘርፉ የኃብት ምንጭ ሆኖ ብዙ ሲሰራበት እንዳልነበረ እና እንደ ሀገር በርካታ ጸጋዎችን እንዲለሙ ማድረግ የተቻለበት አካባቢ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህ ግዙፍ ፓርክ ትልቅ ዕድል ይዞ በመምጣትና የአካባቢውን አቅም በማውጣት ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።

ያለንን ጸጋ እና ኃብት በማልማት ለኢትዮጵያውያን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየሰጡት የሚገኘው የመሪነት ጥበብ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ነው ያሉት።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!