የሀገር ውስጥ ዜና

ፈተናዎች አጠንክረውን በጽናት እንድንሰራና ውጤት እንድናገኝ አድርገውናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Abiy Getahun

October 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት ያየናቸው ፈተናዎች እና መከራዎች አጠንክረውን በበለጠ ጽናት ተግተን እንድንሰራ እና ውጤት እንድናገኝ አድርገውናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ በሚል ርዕስ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ፤ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፣ የሚገባትን ስፍራ ትይዛለች፣ ያንን ስፍራዋን የመያዝ ጉጉት እና ምኞት ግን ከእኛ ጥረትና ድካም ውጪ የሚረጋገጥበት መንገድ አለ ብዬ አላምንም ብለዋል።

በእያንዳንዱ ርምጃ እንማራለን፤ በጥልቀት ለማየት እንሞክራለን፤ ያየነውን ለብዙዎች ለማሳየት እንፍጨረጨራለን በማለት ገልጸው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ትሰራለች ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት ያየናቸውና የተማርናቸው ነገሮች መጀመሪያ ኢትዮጵያን ለማወቅ ነው በማለት ገልጸው፤ የብዙዎች ችግር ኢትዮጵያን አለማወቅ ነው ብለዋል።

በዚህም የተነሳ በትንሽ ሳንቲም ለባዳ ሲገዙ እንደሚታይ ጠቅሰው፤ የትልቅ ሀገር ዜጋ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ጊዜ ሰጥቶ ሀገር በመስራት ውጤት እንደሚያመጣ አስገንዝበዋል።

በጋራ እና በመትጋት መስራት ከተቻለ ምንም ጥርጥር የለኝም ውጤታማ እንሆናለን፤ የኢትዮጵያን ብልጽግናን እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

የጀመርናቸው ስራዎች ሁሉ ፍጻሜ እያገኙ ውጤት እያየን ስለሆነ ፍሬውን ከልጆቻችን ጋር ለማየት ጊዜው ሩቅ አይደለም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ አንዳንድ መስኮች ከተጠበቀው በላይ ስኬታማ እንደሆኑም ተናግረዋል።

የተገኙ ውጤቶች በቀጣይ የሩብ ዓመታት በማስቀጠል ውጤቶችን ማላቅ ከታቻለ የኢትዮጵያን የኃይል ሽግሽግ የሚቀይሩ መሰረታዊ ጉዳዮች የሚከናወኑበት ዓመት እንደሚሆን ተናግረዋል።

ውጤቱን ለማጽናት በለለጠ ትጋት እና አቅም መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook WMCC TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!