አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ100 ቀናት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በሰጡት አስተያየት፤ በሁሉም መስኮች ተስፋ የሚፈነጥቁ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የግብርናው ዕድገት ከሌሎች ዘርፎች ዕድገት ጋር ተሳስሮ በመሠራቱ ተስፋችንን መጨበጥ ጀምረናል ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ፣ የወልመል መስኖ፣ የማዳበሪ ፋብሪካ እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ተስፋችንን መጨበጥ መጀመራችንን ብሎም የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬነት አመላካች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
አፈጻጸሙ እንደሚያስረዳው የተቀመጡ ግቦች በስኬት እየተከናወኑ ነው፤ የግብርናው ዕድገትም በአርሶ እና አርብቶ አደሩ ኑሮ ሁሉ የሚገለጥ ሆኗል ነው ያሉት።
የተመዘገቡት ውጤቶች የተገኙት በፈተና ውስጥ መሆኑ ደግሞ ሀገራችንን ፈተና ሳይበግራት ስኬታማ ጉዞ ማድረግ መቻሏን እንደሚያሳይ አንስተዋል።
አዲስ የሥራ ባህል እየተፈጠረ መሆኑን ዐይቻለሁ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሕዝብን በማሳተፍ ጀምሮ የመጨረስ ዐቅም እያደገ መምጣቱንም ታዝቤያለሁ ብለዋል።