አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካን ከመሳሪያ ድምፅ ነጻ ለማድረግ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል አሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዎስን (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የጣና ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
“አፍሪካ በተለዋዋጩ ሉላዊ ሥርዓት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው ፎረም በአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች እየተደረጉ ነው።
በዚሁ ወቅት ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ባደረጉት ንግግር፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን ማስቆም ቀዳሚ ጉዳይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ለዚህም አስቸኳይ የተግባር ርምጃዎችን ወደ መሬት ማውረድ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በመፃኢው ዓለም አፍሪካን ስኬታማ ለማድረግ በአንድነት እና በትብብር መጓዝ እንደሚያስፈልግ በማብራራት፤ አፍሪካን ከመሳሪያ ድምፅ ነፃ የሆነች ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ጠንካራ ትብብር እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።
11ኛው የጣና ፎረም በትናንትናው ዕለት በባህር ዳር የተካሄደ ሲሆን ዛሬና ነገ በአዲስ አበባ መካሄዱን ይቀጥላል።
በአሸናፊ ሽብሩ