የሀገር ውስጥ ዜና

የፖለቲካ ሥርዓትን ለማዘመን በፉክክርና ትብብር መካከል ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል – አቶ አደም ፋራህ

By Adimasu Aragawu

October 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ሥርዓትን ለማዘመን በፉክክርና ትብብር መካከል ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ።

የአማራ ክልል መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ አቶ አደም ፋራህ፣ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን አየለ፣ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ እንዲሁም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተወከሉና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የፖለቲካ ሥርዓትን ለማዘመን በፉክክርና ትብብር መካከል ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል።

ጤናማና ውጤታማ ፉክክር ከጤናማ የፖለቲካ ምኅዳር የሚመነጭ በመሆኑ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱ የሰጠውን ማዕቀፍ በመጠቀም መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ጤናማ ፉክክር እንዲኖር ለማስቻል የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን ሚና መወጣት እንዲችሉና የሕዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አጀንዳዎችን ይዘው እንዲሠሩ እንዲሁም ሕግና መርህን ማክበር እንደሚኖርባቸውም ነው የተናገሩት።

አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው÷ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክክር የዴሞክራሲ ልምምዳችን ሥር እንዲሰድና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲዳብር የሚያስችል ነው ብለዋል።

ለሰላም፣ ልማትና ሁለንተናዊ የሕዝብ ተጠቃሚነት ሁነኛ ሚና እየተጫወቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ ዴሞክራሲን አደጋ ላይ የሚጥሉ አሰላለፎች የያዙና በኃይል መንግሥትን የመናድ ተግባርና ፍላጎት ያላቸውም መኖራቸውን ተናግረዋል።

ፓርቲዎች የፖለቲካ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚደረግን ፍላጎት በመግታት ዴሞክራሲን በሁለት እግሩ ለማቆም መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።

ፓርቲዎች ሲመሰረቱና ፈቃድ ሲያገኙ የሀገሪቱን ሕግ አክብረው ሊሰሩ የገቡትን ቃል በማክበር ዴሞክራሲያዊ ትግላቸውን ማስቀጠልና ሕግና ሥርዓትን አክብረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የምክክር መድረክ ማካሄዱ የሚበረታታና መልካም ተሞክሮ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን አየለ ናቸው።

ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ ጎን ለጎን የክልሉን ሕዝብ የሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ፍላጎት ለማሟላት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

በደሳለኝ ቢራራ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!