የሀገር ውስጥ ዜና

ሐረር ከተማን ለነዋሪዎች ጽዱ፣ ውብና ምቹ የማድረግ ሥራ…

By Yonas Getnet

October 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ ሐረርን ለማንበር ያለሙ ስምምነቶች ተፈርመው ስራዎች እየተሰሩ ነው አለ የሐርሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት።

ሐረር ከተማ ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነፃ ለማድረግ የተጀመረው ኢንሼቲቭ እያስገኘ ያለውን ውጤት አስመልክቶ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ዕውቅና ተሰጥቷል።

ይህንን አስመልክቶም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ እንዳሉት÷ ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ ሐረርን ለማንበር ያለሙ ስምምነቶች ተፈርመው እየተሠራ ነው።

ከስምምነቶቹ መካከል ኪዩቢክ ፕላስቲክ ፕራይቬት እና የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በፈረንጆቹ ሚያዚያ 2024 የተፈራረሙት እንደሚገኝበት ገልጸው÷ በስምምነቱ መሰረት የሚሰበሰቡ ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ ደረቅ ቆሻሻዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ከሚሰበሰበው ቆሻሻ እስከ 48 በመቶ ያህሉ ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህን እንደገና መልሶ በመጠቀም ከፕላስቲክ በሚሰራ ጡብ የቤት ግንባታ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ለአብነትም ከ500 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በሐረር ከተማ ጁገል አካባቢ ቤተ መጻሕፍት መገንባቱን አንስተዋል።

ሕብረተሰቡን የማስተማር ሥራ መሠራቱን እና በተለይም ሴቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ እስካሁን ከ600 በላይ ሴቶች የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

እየተደረገ ባለው ጥረት በሐረር ከተማ በየአካባቢው ይታይ የነበረው የፕላስቲክ ነክ ደረቅ ቆሻሻ መቀነሱንና አሁን እየተገኘ ያለው ውጤት በቀጣይ ብዙ ለመሥራት አቅም እንደሚሆን አመላክተዋል።

ለዚህ ጥሩ ጅማሮ እና ጥረት በሳንፍራሲስኮ የተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ዕውቅና መስጠቱን በማንሳት÷ ከዕውቅናው በፊት የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በሐረር ተገኝተው ግምገማ ማድረጋቸውን አውስተዋል።

ሕብረተሰቡ ፕላስቲክን በአግባቡ እንዲወገድ የማድረግ ልምዱ እየዳበረ መሆኑን እና ለነዋሪ ምቹና ጽዱ ሐረርን ለማንበር በሚደረገው ጥረት የሕብረተሰቡ ሚና እንዲጠናከር መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!