አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የኃይል ማዕከል በመሆን ቀጣናዊ ትስስርን እያጠናከረች ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
2ኛው የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ÷ ውሃና ኢነርጂ የዘርፎች የሽግግር ሞተር፣ ለኢንዱስትሪ ኃይል፣ ለግብርና ግብዓት እንዲሁም የቤተሰብን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል የነገን ተስፋ የሚያበራ ነው፡፡
የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እየተጠናከረ መሆኑን ጠቁመው ÷ በተለይም በታዳሽ ኃይልና አረንጓዴ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ እየፈሰሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አሁን ላይ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከብክለት የጸዳ የኃይል አማራጭን እየተጠቀሙ ነው ፤ ጎረቤት ሀገራትም እያደገ ካለው የኃይል ልማት ተጠቃሚ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልን ለጂቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ እያቀረበች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በቅርቡም ወደ ሌሎች ሀገራት እንደምትልክ ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዚህ የላቀ ሕልም ማዕከል በመሆን የጽናት፣ የአንድነታችን እና በአፍሪካ መጻኢ የጋራ ትልሞች ላይ ያለን እምነት የሚገለጽበት ነው ብለዋል፡፡
ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ግድብ በመሆን ከአየር ብክለት የጸዳ ኃይልና አህጉራችን በዓየር ንብረት ለውጥ እና ከዘላቂ ልማት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ሕዳሴ ግድብ ጎርፍን በመከላከል እና በታችኛው ተፋሰስ ላሉ ሀገራት ተገቢ የውሃ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ለቀጣይ ከፉክክር ይልቅ የጋራ ተጠቃሚነት ግብን መፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል።
ዓባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ ገናሌ ዳዋ እና ሌሎች ወንዞች የሚከፋፍሉን ድንበሮች ሳይሆኑ የሚያስተባብሩን ድልድዮች ናቸው፤ እኛ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት የአንዱ ብልጽግና ለሁሉም ብልጽግና ነው የሚል ጽኑ እምነት አለን ብለዋል።
ለዚህም ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር በትብብር እና በመነጋገር መስራት አለብን በሚል ጽኑ እምነት እየሰራን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ኢኮኖሚያችን እያደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባሕር በር ማግኘት ለነጋችን ዋስትና የሚሰጥ ነው፤ ይህ ልዩ ጥቅም ለማግኘት መፈለግ አይደለም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር በር ማግኘት ንግድን ያጠናክራል ፤ ለውህደት መሰረት ይጥላል፤ ቀጣናዊ ትብብርንም ያሳድጋል ብለዋል።
በለይኩን ዓለም