አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት ለተለያዩ ዘርፎች ከ262 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ፡፡
ሚኒስትሯ የ2018 ሩብ ዓመት አፈጻጸምን አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት ፥ ባለፉት ሶስት ወራት በፋይናንስ ዘርፍ የተመዘገበው አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በተለይም ዘርፉን አካታች፣ በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ እና አስተማማኝ ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
በዚህ መሰረትም አጠቃላይ የባንኮች ተቀማጭ ሃብት 3 ነጥብ 73 ትሪሊየን ብር መድረሱን ጠቅሰው÷ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ38 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አብራርተዋል፡፡
ለተለያዩ ዘርፎች ከ262 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል ያሉት ሚኒስትሯ ÷ከዚህ ውስጥም 81 በመቶው ለግል ዘርፍ፤18 ነጥብ 7 በመቶው ደግሞ ለመንግስት የተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ በዲጂታል ሥርዓት የተከናወነ ቁጠባ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱን ገልጸው ÷11 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብድር መሰጠቱንም አመልክተዋል፡፡
የፋይናንስ ኢንዱስትሪው የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው የካፒታል ገበያ ወደ ሥራ መግባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
በባንኮች መካከል ከሚደረግ ግብይት አንጻር የካፒታል ገበያ 200 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን አስረድተዋል፡፡
8 ነጥብ 29 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን ጠቁመው ÷ ከዚህ ውስጥም የወጪ ንግድ 57 ነጥብ 6 በመቶውን እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ አንጻር ብሄራዊ ባንክ 150 ሚሊየን ዶላር ያጫረተ ሲሆን ÷ ባንኮች ደግሞ 19 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ተገበያይተዋል ነው ያሉት፡፡
በመላኩ ገድፍ