አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጪ ንግድ ሸቀጦች ከአገልግሎት የበለጠ ውጤት አምጥተዋል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት እየተካሄደ ባለው 6ኛ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ነው።
ባለፈው ዓመት ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም በአገልግሎት 8 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል፣ የዘርፎችን ምርታማነት እንዲሁም የመወዳደርና የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ የመንግስት ትልቁ ዓላማ መሆኑንም አመላክተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዘላቂ የፋይናንስ ስርዓትን መዘርጋት፣ የኢትዮጵያ አቅም ተጠቅሞ ሀገር መለወጥ እንዲሁም አንድም ብድር ከውጭ ሳይመጣ ኢትዮጵያን ማሳደግ እንደሚቻል አሳይቷል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ነበር፤ ይህንን ለመቀየር ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።
የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ በሬሚታንስ 7 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም በቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ መገኘቱን ገልጸው÷ ባለፈው ዓመት በርካታ ሌሎች ዘርፎች ያስገኙትን ጨምሮ በታሪክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገኘበት እና መጠባበቂያም የጨመረበት መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እድገት ለመላው አፍሪካ ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ጥሩ ዓይንና ጆሮ ያለው ሰው የኢትዮጵያን ለውጥ ማየት እና መመልከት ይችላል፤ ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያ አድጋ ጨርሳለች ማለት አይደለም ሲሉም አስገንዝበዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!