የሀገር ውስጥ ዜና

የባሕር በር ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው – አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

October 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው አሉ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)።

አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) ለፋና ዲጅታል እንዳሉት÷ ከ30 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ለማዳከም በሚፈልጉ የውስጥና ውጪ ኃይሎች ሴራ ሀገሪቱ የባሕር በር አጥታለች።

በወቅቱ የተፈጠረውን ስህተት ለማስተካከል ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለው የባሕር በር ጥያቄ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷን ለማስከበር ያነሳችው እንደሆነ አመላክተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የባሕር አጠቃቀም ስምምነት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እንደሚደግፍ ገልጸው÷ ሀገራት ያላቸው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ዕጣ ፈንታቸውን ሊወስን እንደማይገባና የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን የመብት ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት አለመሆኗ ሸቀጦችን ለማስገባት እና ለማስወጣት በምታደርገው እንቅስቃሴ ወጪውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር በማድረግ ዕድገቷ ላይ አሉታዊ ሚና እንደሚጫወት አንስተው÷ ኢንቨስተሮችም በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ እንደ ችግር የሚያነሱት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የገቢና ወጪ ሸቀጦችን ደህንነት ኢትዮጵያ በራሷ ቁጥጥር ስር አለመሆንና በሌላው አካል ቁጥጥር ስር ሆኖ መቀጠሉ አደጋ እንደሚሆንም አንስተዋል።

የባሕር በር ማግኘት የቀጣናውን ሰላም እና ደህንነት በማስጠበቅ የአካባቢውን ሀገራት ብሎም ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ተጠቃሚ ያደርጋልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ያቀረበችው በሰላማዊና ሰጥቶ መቀበል መርህ ባሕር በር የማግኘት ጥያቄ አሁን ላይ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ እየታወቀ የመጣ አጀንዳ በመሆኑ በርካታ ሀገራት እየደገፉት መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በሕብረት እንዳሳካነው ሁሉ የባሕር በር ጉዳይንም ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!