ስፓርት

ካለፉት 7 ጨዋታዎች በስድስቱ የተሸነፈው ሊቨርፑል…

By Adimasu Aragawu

October 31, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል በሁሉም ውድድሮች ካደረጋቸው ያለፉት ሰባት ጨዋታዎች በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡

ከእነዚህም መካከል አራት ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገደው ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ነው፡፡

ከሊጉ ጨዋታዎች በተጨማሪ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ በጋላታሳራይ የተሸነፉት ቀዮቹ፥ በካራባኦ ካፕ በክሪስታል ፓላስ ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል፡፡

በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው ያለፉት ሰባት ጨዋታዎች 14 ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን፥ ባለፉት 10 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት አልቻለም፡፡

አንፊልድ ሮድ ስታዲየም ተጋጣሚ ቡድኖች የሚፈሩትና የሚረበሹበት ቢሆንም አሁን ግን ተቃራኒ ቡድኖች ከአንፊልድ በተደጋጋሚ ነጥብ ይዘው እየወጡ ይገኛል፡፡

የወድድር ዘመኑ ከመጀመሩ አስቀድሞ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ወደ ስብስቡ የቀላቀላቸውን ተጫዋቾች በመመልከት ሊቨርፑል አስቸጋሪ ጊዜ ያሳልፋል ተብሎ አልተጠበቀም ነበር፡፡

የመርሲሳይዱ ክለብ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከ400 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ለተጫዋቾች ዝውውር ቢያወጣም አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች የተጠበቁትን ያህል እየተንቀሳቀሱ አይገኝም፡፡

የፕሪሚየር ሊጉን የዝውውር ክብረ ወሰን ሰብሮ አንፊልድ የደረሰው አሌክሳንደር አይዛክ፣ ፍሎሪያን ቪርትስ እና ሁጎ ኢኪቲኬ እያሳዩት ባለው እንቅስቃሴ ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል፡፡

እንዲሁም ሊቨርፑል አምና የሊጉን ዋንጫ ሲያሳካ ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከተውና የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰው ሞሀመድ ሳላህ በዚህ የውድድር ዓመት እያሳየ ባለው ደካማ አቋም እየተተቸ የሚገኝ ተጫዋች ነው፡፡

በሰባት ቀናት ውስጥ ሶስት ጨዋታዎችን ለማድረግ መገደዳቸውን በመግለፅ የጨዋታ መደራረብ እንዳለባቸው የገለጹት አሰልጣኝ አርኔ ስሎት፥ ነገር ግን ለውጤት ቀውሱ እንደ ሰበብ ማቅረብ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ የክለቡና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እስጢፋኖስ ዋርኖክ በቢቢሲ ራዲዮ በሰጠው አስተያየት፥ አሰልጣኙ የጨዋታ መደራረብ እንደሚኖርና የቡድኑ ጥልቀት ጥሩ እንዳልሆነ ቀድመው ተረድተው በዝውውር መስኮቱ ከዚህ በበለጠ መሳተፍ ነበረባቸው በማለት አሁን ሰበብ ማብዛት አስፈላጊ አይደለም ሲል ተችቷል፡፡

ከፊቱ ፈታኝ ጨዋታዎች የሚጠብቁት ሊቨርፑል በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር አስቶን ቪላን፣ በሻምፒየንስ ሊጉ ደግሞ ሪያል ማድሪድን በሜዳው የሚያስተናገድ ሲሆን ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከማንቼስተር ሲቲ ጋር ይፋለማል፡፡

በመጀመሪያዎቹ አምስት ሳምንታት በሊጉ ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ሊጉን ከአርሰናል በአምስት ነጥብ ልዩነት ሲመራ የነበረው ሊቨርፑል አሁን ከሊጉ መሪ አርሰናል በ7 ነጥብ ርቆ በ15 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ወደ አንፊልድ በመጡበት ዓመት ከሊቨርፑል ጋር የሊጉ ባለ ክብር መሆን የቻሉት አርኔ ስሎት ለዘንድሮው የሊጉ ክብር በቀዳሚነት የተገመተውን ሊቨርፑል ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የመመለስ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ