አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን አቅፋ ይዛለች፡፡
የ13 ወር ጸጋ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ባሏት ውብ ተፈጥራዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች የዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ትታወቃለች፡፡
በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችንም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ ና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) አስመዝግባለች፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ቱባ ባህልና ትውፊት እንዲሁም ቅርሶች በውጪው ዓለም በሚገባ ማስተዋወቅ ላይ ውስንነቶች እንዳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ዓለም አቀፍ የባህል ፌስቲቫል አዘጋጁ ሚኪያስ ሙሉጌታ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የሕብረ ብሄራዊነት መገለጫ የሆነችው ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትና የአፍሪካ የድል ተምሳሌት ናት፡፡
የኢትዮጵያን ቱባ ባህሎች፣ እሴቶች፣ ትውፊቶች፣ ቋንቋዎች፣ ኪነ ጥበባት እና ሀገር በቀል እውቀቶች በውጪው ዓለም በሚገባ ማስተዋወቅ የሕዝብ ለሕዝብ ብሎም የባህል ትስስርን ለማጠናከር ያግዛል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦችን የአኗኗር ዘዬ፣ ባህላዊ ምግቦች፣ አልባሳት፣ ውዝዋዜ፣ ጌጣጌጦች፣ የቡና አፈላል ሥርዓት እና ሌሎችን በውጭ ሀገራት ለማስተዋወቅም የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በቅርቡ እንደ አዲስ የተጀመረው የኪን ኢትዮጵያ ተግባር አበረታች መሆኑን ገልጸው ÷ መሰል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
እንደ ዓለም አቀፍ የባህል ፌስቲቫል አዘጋጅነታቸውም የኢትዮጵያን ቱባ ባህል እና ትውፊት በተለያዩ የዓለም መዳረሻዎች እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በእንግሊዝ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም በአሜሪካ በሚዘጋጁ የባህል ፌስቲቫሎች ላይ የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳዩ የኪነጥበብ ሥራዎችን እንዳቀረቡ ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያን ባህል በውጪው ዓለም በሚገባ ለማስተዋወቅ የባህል ፌስቲቫል መድረኮችን በውጪ ሀገራት በቋሚነት ማዘጋጀትና በድግግሞሽ ማሳየት እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡
ባህሎችን እና የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ የጥበብ ባለሙያዎች በአካል መገኘት ተመራጭ መሆኑን ጠቅሰው ÷ ለዚህ ሒደትም ቪዛና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ኤምባሲዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በአረንጓዴ ዐሻራ በአየር ንብረት ለውጥ ያከናወነቻቸው ሥራዎች እውቅና ማግኘታቸውን ጠቁመው ÷ ይህን ተከትሎም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ ኢትዮጵያ ትልቅና ልዩ ቦታ እንደሚሰጣት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሰራችውን አስደናቂ ሥራ ከባህል ጋር በማስተሳሰር ይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ የኪን ኢትዮጵያን አላማ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ÷ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ባህልና ትውፊት በውጭ ሀገራት ለማስተዋወቅ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ኪን ኢትዮጵያ ሕብረ ብሄራዊትና የራሷ ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያ ባህል፣ ኪነጥበበ፣ ዕደ ጥበብ፣ እውቀት እና ልዩ ክዋኔዎች ለዓለም የማስተዋወቁ ሒደት አበረታች መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ጉዞ ከ39 ዓመታት በኋላ የተጀመረ ታሪካዊ ጉዞ ሲሆን÷ ከ50 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃዎችና ጥበባት እንደሚቀርቡበት ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በጉዞው ከትርኢቶች ባሻገር ኢትዮጵያ የአልባሳት ዲዛይን፣ የቡና ቅምሻ እና የአመጋገብ ባህሏን ታስተዋውቅበታለች ነው ያሉት።
በተለያዩ መልኩ ባህል፣ ኪነጥበበ፣ ዕደ ጥበብ፣ እውቀት እና ልዩ ክዋኔዎች ለዓለም ለሚያስተዋውቁ አካላት አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ