አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ለተገልጋዮች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ከበደ ሻሜቦ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ባለ ጉዳዮች ጊዜያቸውና ገንዘባቸው ሳይባክን ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ህብረተሰቡ አገልግሎት ለማግኘት ወደተለያዩ ተቋማት ለአላስፈላጊ ወጪ ይዳረግ እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ላይ በአንድ ጣሪያ ስር የተቀናጀና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ በሁሉም አገልግሎቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣና ችግር ፈቺ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተገልጋዮች ክፍያ የሚፈፅሙበት በዲጂታል ሥርዓት መኖሩ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚያስቀር መሆኑን ገልጸው፥ ህብሰረተሰቡ ወደ ማዕከሉ በመምጣት ያለ ተጨማሪ ወጪ እና እንግልት ፈጣን አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት ይችላል ብለዋል፡፡
ሰባት ተቋማት በማዕከሉ እንደሚገኙና 20 ያህል አገልግሎቶች ለማህበረሰቡ እየተሰጡ ሲሆን፥ በቀጣይ በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ 60 ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክልሉ በአምስት ከተሞች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ