አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት ግምቱ 38 ሚሊየን ብር የሆነ 4 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም ወርቅ በህገ ወጥ መንገድ ሲሸጥ የተያዘው ግለሰብ በእስራት እና በገንዘብ እንዲቀጣ ወሰነ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ሆሞሻ ወረዳ ነዋሪ የሆነው መሀመድ ሳሊህ መሀመድ ላይ ክስ የመሰረተው በፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ነው።
ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ግለሰቡ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 6 ሰዓት ሲሆን በአሶሳ ከተማ ልዩ ስሙ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ በተደረገ ክትትል በተሰጠው የወርቅ አቅራቢነት ፍቃድ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ለሰጣቸው አካላት ብቻ ወርቁን መሸጥ ሲገባዉ በባንክ ፍቃድ ላልተሰጠው አካል ወርቅ ለማስተላለፍ ሲሞክር እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡
ግለሰቡ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-3280B አ.አ በሆነ ተሸከርካሪ ውስጥ ከብሔራዊ ባንክ ወይም ባንኩ ፍቃድ ከሰጣቸው አካል ውጪ አንዱን ግራም በ8 ሺህ 400 ብር አጠቃላይ 4 ሺህ 600 ግራም ወይም 4 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም የሆነ የወርቅ ምርት በ38 ሚሊየን 640 ሺህ ብር ፍቃድ ላልተሰጣቸው ግለሰቦች ለመሸጥና ለማስተላለፍ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉ በክሱ ተዘርዝሯል።
ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን እንዳልፈጸመ በመግለጽ ክዶ ተከራክሯል።
ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሹን እንዲሁም ሌሎችን ያስተምራል በሚል በ3 ዓመት ከ7 ወር ፅኑ እስራት እና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ እንዲሁም የተያዘዉ 4 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም ወርቅ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ወስኗል።
በሲፈን መኮንን