አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተፈጠረው ንጋት ሰው ሰራሽ ሐይቅ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዓሣ ሀብት ልማት ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የንጋት ሐይቅ መፈጠር የክልሉን የዓሣ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
ከዚህም ባለፈ ሰፊ የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ በሐይቁ ላይ በዓሣ ማምረት ስራ የሚሰማሩ 78 ማህበራት ተደራጅተዋል ብለዋል።
ማህበራቱ ወንድ 735 ሴት ደግሞ 154 በድምሩ 889 አባላት እንዳላቸው ገልጸው፤ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት 557 አባላት ያሏቸው 35 ማህበራት ወደ ስራ ገብተዋል ነው ያሉት።
ማህበራቱ ዓሣ በማምረት ለገበያ ማቅረብ እንደጀመሩ ጠቅሰው፤ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ 1 ሺህ 435 ቶን ዓሣ ማምረታቸውን ተናግረዋል።
ቀጣዮቹ ወራት ለዓሣ ማምረት ተግባር ምቹ በመሆኑ በሁለተኛው እና በሶስተኛው ሩብ ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።
የክልሉ መንግስት የዓሣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የገበያ ትስስርን ለማጎልበት ከግብርና ሚኒስቴር እና ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የማህበራቱን የቁሳቁስ ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን በማንሳት 48 የእንጨት ጀልባ፣ ስድስት የሞተር ጀልባ፣ 1 ሺህ 600 ጥቅል የመረብ መስሪያ ክር እንዲሁም 1 ሺህ መረብ ተሟልቷል ብለዋል።
የዓሣ ምርቱን ለተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግ ፍሪጅ እና ማቀዝቀዣ የተሟላለት ተሽከርካሪ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
በአቢይ ጌታሁን
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!