ቢዝነስ

የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እየሆነ የመጣው የሮዝመሪ ቅመም …

By Adimasu Aragawu

November 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሮዝመሪ ቅመም የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እየሆነ መጥቷል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የሮዝመሪ ቅመም ልማት በክልሉ ከተጀመሩ አዳዲስ ኢኒሼቲቮች መካከል አንዱ ነው።

ሮዝመሪ ከዚህ በፊት በስጋ መጥበሻነት ብቻ እንደሚታወቅ አስታውሰው÷ አሁን ላይ በአሲዳማነት ችግር ተጎድተው ምርታማነታቸው በቀነሱ አካባቢዎች ላይ በስፋት እየለማ መምጣቱን ተናግረዋል።

የሮዝመሪ ልማት በአሲዳማነት የተጎዳ መሬትን በማከም እና ለአልሚዎች ገቢ በማስገኘት ለሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ እየሆነ መጥቷልም ነው ያሉት።

እንደ የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን መረጃ፤ በክልሉ በቤተሰብ ደረጃ አንድና ከዚያ በላይ ቅመም መመረት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

የባለስልጣኑ ቡናና ቅመማ ቅመም ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተፈራ ዘርፉ÷ ይህ አቅጣጫ የክልሉን የቅመማ ቅመም ምርታማነት እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም ዘር የማባዛት ስራ በማከናወን በ2013 ዓ.ም 326 ሄክታር የነበረውን የሮዝመሪ ቅመም ሽፋን በአሁኑ ወቅት ከ17 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መድረሱን ጠቁመው÷ ከ10 ሺህ 300 በላይ ሄክታር መሬት ላይ ያለው ሮዝመሪ ምርት መስጠት ጀምሯል ብለዋል።

የሮዝመሪ ቅመም ሌሎች ሰብሎችን ማምረት በማይቻልበት ቦታ ላይ አሲዳማ አፈርን በመቋቋም ምርት መስጠት የሚችል ሰብል በመሆኑ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደግ መምጣቱን አስረድተዋል።

በክልሉ ከ30 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሮዝመሪን ሰብል በማምረት ስራ ላይ መሰማራቱን የገለጹት አቶ ተፈራ÷ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።

በ2014/15 የምርት ዘመን ለሀገሪቱ 725 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገኘቱን አስታውሰው÷ ይህም እያደገ በመምጣት ባለፈው ዓመት 5 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት መቻሉን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት ከ224 ሺህ ኩንታል በላይ የሮዝመሪ ምርት መገኘቱን ገልጸው÷ በዚህ ዓመት ከ280 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!