የሀገር ውስጥ ዜና

በሲዳማ ክልል ለኮሪደር ልማት የኤሌክትሪክ መስመርና ትራንስፎርመር ማዛወር ሥራ እየተከናወነ ነው

By Melaku Gedif

November 07, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ ማድረግ የሚያስችል የመልሶ ግንባታና ማሻሻያ ሥራዎች ተከናውነዋል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የተከናወነው የመካከለኛ የኃይል መስመር ዝርጋታ መልሶ ግንባታ ሥራ 103 ነጥብ 465 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡

በዚህም 995 የእንጨት ምሰሶ እና 1 ሺህ 75 የኮንክሪት ምሰሶ በአጠቃላይ 2 ሺህ 70 የኃይል መስመር የተሸካሚ ምሰሶዎች ተከላ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡

የመልሶ ግንባታ ሥራው ከሀዋሳ እስከ ወንዶ ገነት፣ ከዋራ እስከ አንፌረራ፣ ከይርጋለም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ለኩ ከተማ እንዲሁም ከይርጋለም እስከ ሎካ እና አባያ ያሉትን መስመሮች የሚሸፍን ነው፡፡

በተጨማሪም ከአለታ ወንዶ እስከ ሀገረ ሰላም እና ጋስ ቀበሌ ከተማ ድረስ ያለውን የኃይል መስመር ይበልጥ ለማሻሻል የመልሶ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በሀዋሳ፣ ይርጋለም እና ወንዶ ገነት ከተሞች ላይ ለሚከናወነው የኮሪደር ልማት የመስመር ማዛወር ሥራ 743 የመስመር ተሸካሚ ምሰሶዎችና 17 ትራንስፎርመሮችን የማዛወር ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡

በኮሪደር የመስመር ማዛወር ሥራው ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ በተዘጋጀው ቦታ ላይ 9 ነጥብ 15 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር እንዲሁም 16 ነጥብ 9 የዝቅተኛ መስመር የመልሶ ግንባታ ሥራ ተሰርቶ ተጠናቅቋል፡፡

በተጨማሪም በሀዋሳ ከተማ ከሳውዝ ስፕሪንግ እስከ ሀይሌ ሪዞርት እና ሻፌታ ድረስ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በመሬት ውስጥ ተቀባሪ መስመር ዝርጋታ ሥራ ለማከናወን የፒፒሲ ቀበራ ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ