አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎንደር ከተማ ከአዘዞ እስከ ፒያሳ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ጎንደር ዳግም ለመወለድ እያማጠች መሆኑን ያሳያል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የታደሰውን የፋሲል አብያተ መንግሥት ጊቢ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ፋሲል ብንዞር ብንዞር በቀላሉ የማናገኘው፤ እኛ በእጃችን ያለንን የማርከስ ክፉ አባዜ ስላለብን የረከሰ ታላቅ ወርቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህን የመሰለ ስጦታ የሰጡን አባቶቻችንን ፈለግ ተከትለን ሀገር ብናለማ እና ብንሰራ ዛሬ ኢትዮጵያ ተረጂ እና ለማኝ አትሆንም ነበር ነው ያሉት፡፡
ትልቁ ችግራችን እናንስና ትልቁን ጎትተን በማሳነስ መተካከል እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ከእነዚህ ታላላቅ መሪዎች በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው ችግር ያነሱ፣ ትላልቁን ደግሞ ጎትተው የሚያሳንሱ መበራከታቸው ነው ብለዋል፡፡
ታላቆችን ማክበር፣ የታላቆችን ሥራ ማድነቅና መመርመር ሲጀመር በዚያ ሥራ ላይ አንድ ጡብ ባስቀምጥ መባሉ አይቀርም፤ ታላላቆችን ማሳነሰ ሲጀመር ግን የማናድግ፤ ያደገውን የምናሳንስ ተያይዘን የምናጥር ያደርገናል ነው ያሉት፡፡
የኋላ ታሪኩን ማስታወስ የቻለ ሰው ወይም ማሕበረሰብ ዛሬን ለመነሻነትና ለመስሪያነት ይገለገላል፤ ዛሬን መነሻ ያላደረገ ደግሞ የተንደረደረ ነገር ማየት አይችልም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በጎንደር ከተማ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲሁም በፋሲል ጊቢ ውስጥ በተሰራው ሥራ ልጆቻችን ከእኛ የተሻለ ተስፋ እንዳላቸው ማሰብ ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ ተስፋ ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡
የጎንደር ታዳጊዎች ከፊታችሁ ያለው ዘመን ብሩህ ስለሆን አባቶቻችሁ ገንብተዋል፤ እኛ ለማቆየት ሞክረናል፤ አልቃችሁ ጎንደርን ብትሰሩ ደግሞ የበለጠ የለማና የተዋበ ሀገር መፍጠር ይቻላል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ስለሆነም ልቦናችሁን ሰብሰብ አድርጋችሁ ጎንደርን ድጋሚ ለመውለድ በጋራ መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ፋሲልን ከ30 ዓመት በፊት አውቀዋለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ተጠገነ የሚለው ስም ያንስበታል፤ ዳግም ተወለደ ቢባል ተገቢ እንደሚሆን አውስተዋል፡፡
ጎንደር ከተማ ልክ እንደ ፋሲል አብያተ መንግሥት ራሷን ዳግም ወልዳ ማየት የሁላችንም መሻት፣ ምኞትና ሥራ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ከአዘዞ አንስቶ እስከ ፒያሳ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራም ጎንደር ዳግም ለመወለድ እያማጠች መሆኑን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል፡፡
ሥራውን ደግፈንና አግዘን እውን ካደረግነው ልክ በፋሲል ቅጥር ጊቢ እንደሚታየው ያለ ውበት በመላ ጎንደር ከተማ ሊታይ ይችላል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በሌላው ጉዳይ ብንለያይ እንኳን ጎንደርን ዳግም በመስራቱ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም መያዝ አለብን ብዬ በጽኑ አምናለሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡
በመላኩ ገድፍ