አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሀገር ሆና ተመርጣለች፡፡
በኡዝበኪስታን ሳማርካንድ እየተካሄደ በሚገኘው 43ኛው የዩኔስኮ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ አባል ሀገር ሆና የተመረጠችው፡፡
የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ እያንዳንዳቸው አራት ዓመት የሥራ ዘመን ያላቸው 58 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን፥ ኢትዮጵያ እስከ ፈረንጆቹ 2029 አባል ሆና እንደምትቀጥል ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ጉባኤውና ሴክሬታሪያት በተጨማሪ በዩኔስኮ ከሦስቱ መሠረታዊ አካላት አንዱ በሆነው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ቆይታዋ ለተቋሙ የጋራ ውጤት ከሌሎች ሀገራት ጋር በቅንጅት እንደምትሰራ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም እንደ አህጉር የመላው አፍሪካን ጥቅም ለማስጠበቅና ከዩኔስኮ ዓላማና ተልዕኮ አንጻር በባለብዙ መድረኮች ድምጿን ለማሰማት መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።
ለተቋሙ የሥራ መርሐ ግብርና በዋና ዳይሬክተር የቀረበለትን ተጓዳኝ የበጀት ግምት በመመርመር ከውሳኔዎቹ ጋር ለጠቅላላ ጉባኤ ማቅረብ የቦርዱ ኃላፊነት መሆኑም ተገልጿል፡፡