አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “ጭንቅላቱን በመታው የፈንጂ ፍንጣሪ ምክኒያት ፊቱ በረጋ ደም ተሸፍኗል። መላ ሰውነቱ ከተንከባለለበት ጭቃ ጋር ተመሳስሏል፤ የጠየቀኝ ውሃ ነው። ልጄ ውሃ አጠጣኝ ነው ያለው። በኮዳዬ ከቀዳሁት ቆሻሻ ወራጅ ውሃ ሰጠሁት፤ ልጄን ሸዋዬን አጣሁት ሲል ግን በድንጋጤ ራሴን ስቼ ወደኩ።”
መነን አካባቢ ተወልዶ ያደገው የሸዋጌጥ ጫኔ ከአዲስ አበባ እስከ ኤርትራ ከምጽዋ እስከ ሱዳን ድረስ የተዘረጋውን ታሪክ እንደ ትናንት ቅርቡ ሆኖ ይታየዋል።
ገና በታዳጊነት ዕድሜው በልቡ የታቆረው ለሀገሩ ወታደር የመሆን ፍቅር ገንፍሎ ምልመላውን እንደምንም በማለፍ የውትድርናን ዓለም የዛሬ 38 ዓመት 1979 ዓ.ም ሐምሌ 4 ቀን ወደ አስመራ በመጓዝ ሀ ብሎ ጀመረ።
በአስመራ ቃኘው ስቴሽን መሰረታዊ የውትድርና ስልጠናን ያጠናቀቀው የሸዋ ጌጥ ወደ ሙዚቃ ክፍል በመመደብ በዋናነት ክላርኔት ከዚያም በድራም ተጫዋችነት ሲያገለግል ቆይቶ ሳክስፎን ግን የመጨረሻ ማረፊያው ሆነ።
ከአስመራ ተነስቶ ደንጎሎን፣ ዲጋ ጋሕተላይ፣ ዶጋሌን በጠመዝማዛና ተራራማ መንገዶችን አልፎ ምጽዋ የተጓዘው ወጣቱ ወታደር ቀይ ባሕር ላይ እየዋኘ ከሠራዊቱ ጋር በባሕር ዳርቻ ያሳለፈው የፈገግታ ታሪክ በዓይነ ኅሊናው ውልብ ይሉበታል።
ነገር ግን በኤርትራ ቆይታው የስቃይ ገፅም እንደነበረው በማስታወስ በዳህላክ ደሴት የሰፈረውን ሠራዊት ለማበረታታት ለማለት ከጓዶቹ ጋር በኦራል ሲጓዙ በዓርበ ሮብዕ ጠመዝማዛ መንገድ ባጋጠማቸው አደጋ ከሙሉ ባልደረቦቹ ሁለት ሰው በሕይወት ሲተርፍ አንዱ እርሱ እንደነበር ይናገራል።
ጊዜውን ሲያስታውስም ዛሬ ቆሜ የምሄደው ከፈጣሪ በታች የወቅቱ ብቸኛ የአጥንት ስቴሻሊስት ጄነራል ዶ/ር ጋጋ ኦልጆ የተሰባበረ የእግሬን አጥንት ለቃቅመው ጠግነው ስለሰሩልኝ ነው በማለትም ይገልጻል።
በመንግስት ሰራተኝነት የሚተዳደሩት ወላጅ አባቱ አቶ ጫኔ ደረሰ ልጄ የሚሞትበት ሂጄ ልሙት ብለው በወዶ ዘማችነት ኤርትራ መግባታቸውን በማስታወስም አንድ ቀን መገናኘታቸውን ነገር ግን ወደየምድባቸው ሲሄዱ ተለያይተው መቅረታቸውን ያስረዳል።
1983 ዓ.ም ነገር ሁሉ ተበላሸ፤ ሻቢያ ድል ቀናው፤ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች እስከ ህቅታ ድረስ ተዋግተው በክብር ወደቁ።
ዛሬ ላይ ቀይ ባሕር፣ ምፅዋ፣ አሰብ ሲባል ተራ የፖለቲካ ማጣፈጫ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህ በሮች ሀገሬ እንደልቧ የምትጠቀማቸው መግቢያና መውጫዋ ነበሩ የሚለው የሸዋጌጥ÷ ምስክሮቹ እኛ በሕይወት ያለነው ሳንሆን ሀቋን ይዘው የተሰውት ደመ ሞቃት ልጆቿ እንደሆኑ በማንሳት ነው።
ቀይ ባሕር እንደ ጀነራል ተሾመ ያሉ ጀግኖች ሽጉጣቸውን የጠጡለት፤ በሠንደቋ ተጠቅልለው ባህር የገቡለት፤ የኢትዮጵያ ሀብትና መብት የሆነ ስፍራ ነው በማለትም በቁጭት እንባ እየተናነቀው ይናገራል።
የአሰብ እና ምፅዋ አሸዋማ መሬት የረሰረሰው በኢትዮጵያ ጀግኖች ደም ነው፤ ምድሩ ቢማስ የሚገኘው የክቡራኑ አጥንት ነው።
የሸዋጌጥ የእናቴ አምላክ መራኝ ሲል በሚተርከው ጉዞው ያለምግብ እና ውሃ 19 ቀናትን በእግሩ ተጉዞ ሱዳን የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ገባ።
በወዶ ዘማችነት ወደ ጦር ግምባር ያመሩት ወላጅ አባቱ ባሬንቱ ላይ ሻቢያ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ትጥቅ ለመንጠቅ ሲል አሰልፎ በሚረሽንበት ወቅት በፈንጂ ቢመቱም በተዓምር ተርፈው ሱዳን የደረሱት ዝናብ ካጨቀየው መሬት እየታገሉ ማንነታቸው እስካይለይ ድረስ ከጭቃው ጋር ተመሳስለው ነበር። በወደቁበት ውሃ ሲቀዳ ያዩትን ልጅ ነው ልጄ ውሃ አጠጣኝ ያሉት።
በጥም ስፍራ ውሃ ያለው ሞት ቢመጣ እንኳን አሳልፎ አይሰጥም፤ እርሱ ግን ስስት አልነበረውምና ኮዳውን ዘንበል አድርጎ አጠጣቸው፤ ጥማቸውን አስታግሰው እንዲህ አሉ “ልጄን ሸዋዬን ተነጠኩ”።
የሸዋጌጥ አባቱን ከደረሰባቸው ጉስቁልና እና ጉዳት አንፃር አይቶ ባይለያቸውም ስሙን ሲጠሩ፤ ልጄ የሚሞትበት ሄጄ ልሙት ብለው ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው የዘመቱት ወላጅ አባቱ አቶ ጫኔ ደረሰ መሆናቸውን አወቀ።
በስደት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጓዶች አቶ ጫኔ እና የሸዋጌጥን ከወደቁበት አነሱ፤ አባትና ልጅ ተገናኙ በማለት በካምፑ ውስጥ ሆታ ሆነ። ከስድስት ወራት የካምፕ ቆይታ በኋላ ጥቅምት 27 ቀን 1984 ዓ.ም አባትና ልጅ ተያይዘው አዲስ አበባ ገቡ።
አባት ወደቀድሞ የመንግስት ስራቸው ሲመለሱ ልጅ ሳክስፎኒስት የሸዋጌጥ ጫኔም ወደ ምድር ጦር ተመለሰ። ነገር ግን የኢትዮጵያና የቀይ ባህር መለያየት ለሸዋጌጥ የልብ ሸክሙ ሆኖ ይኸው ዛሬ ድረስ ዘለቀ። …ነገስ?
በመታገስ አየልኝ
የፋና ላምሮት ሙዚቀኛ የሆነ የሸዋጌጥ ጫኔ ጋር የተደረገውን ቆይታ ከማስፈንጠሪያው ላይ ይከታተሉ👇