አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከመኸር እርሻ እስካሁን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ በመኸር እርሻ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል፡፡
አሁን ላይ አብዛኛዎቹ ሰብሎች ለመሰብሰብ መድረሳቸውን ጠቁመው ÷ እስካሁንም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
የሰብል አሰባሰቡ በኮምባይነር እና በተለያዩ አነስተኛ የሰብል መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ብክነትን በመቀነስ መሰብሰብ እንዳለበት ጠቅሰው ÷ ለዚህም የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የአየር ጸባይ ትንበያ መረጃዎችን በትኩረት በመከታተል የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ ጊዜውን ጠብቆ መሰብሰብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሰብል አጨዳ፣ በመከመርና ውቂያ ወቅት ሊደርስ የሚችልን የምርት ብክነት ለመቀነስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በ2017/18 መኸር እርሻ ከለማው አጠቃላይ ሰብል 187 ሚሊየን ኩንትል ምርት እንደሚጠበቅ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
በመላኩ ገድፍ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!