የሀገር ውስጥ ዜና

የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው

By Adimasu Aragawu

November 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን።

በባለስልጣኑ የቡናና ቅመማ ቅመም ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተፈራ ዘርፉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የቡና ምርታማነቱና ጥራቱ እንዲሻሻል በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ እስከ ክህሎት ስልጠናና ገበያ ትስስር የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2007 ዓ.ም 7 ሺህ ሄክታር የነበረው የቡና ሽፋን አሁን ላይ 165 ሺህ ሄክታር በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

ምርታማነቱን በተመለከተም በተመሳሳይ ዓመት ከሄክታር 4 ነጥብ 6 ኩንታል ምርት ከሚገኝበት አሁን ላይ በተሰራው ስራ 7 ነጥብ 8 ኩንታል መድረሱን አመላክተዋል።

ለአርሶ አደሩ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት፣ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን መትከል፣ የቡና ልማትን በኩታገጠም እንዲታረስ አቅጣጫ ተቀምጦ መስራት ለምርታማነቱ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ነው የገለጹት።

በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ከ40 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ እየተተከለ መሆኑን አንስተው÷ ለዚህም ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትልቅ ሚና መጫወቱን አቶ ተፈራ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደል፣ ተባይና በሽታ ያጠቃቸውን በባለሙያዎች በመለየት ነቅሎ የማቃጠል፣ ባለፈው ዓመት የተተከሉትን የመንከባከብ እንዲሁም አዳዲስ ችግኞችን ለቀጣይ ተከላ ወቅት የማዘጋጀት ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩም አብራርተዋል።

በአድማሱ አራጋው