የሀገር ውስጥ ዜና

ባልተፈቀደ የውጭ ሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ በተሰማሩ አካላት ላይ ርምጃ ተወሰደ

By Yonas Getnet

November 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር ባልተፈቀዱ የውጭ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራዎች ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የተቀናጀ ርምጃ መውሰድ ጀምሯል።

ባንኩ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት በመጠቀም ድንበር ዘለል የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባራትን በሚፈጽሙ ደላሎችና ገንዘብ አቅራቢዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድን የሚያካትት እንደሆነ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

እየተወሰደ የሚገኘው ርምጃ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓት ተአማኒነትን ለመጠበቅና የውጭ ምንዛሪ ፍሰት በሕጋዊ፣ ግልጽና መደበኛ በሆኑ መንገዶች መከናወኑን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት የሚያንጸባርቅ ነው።

ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመፈጸም መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓትን መጠቀም የውጭ ምንዛሪ ገበያን ተአማኒነት የሚያኮሰስና የሀገሪቱን የገንዘብ ሥርዓት አደጋ ላይ የሚጥል አካሄድ እንደሆነ በማንሳት የማስተካከያ ርምጃዎቹ ሕገ ወጥ የሐዋላ ዝውውርን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት አካል መሆናቸውን አብራርቷል።

ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ላልተገባ ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልጉ አካላትን በመለየት ተገቢ ርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

አንዲሁም ባንኩ የውጭ ሐዋላ ፍሰት መደበኛ አካሄድን ተከትሎ አንዲፈጸም የሚረዱ ርምጃዎችን ለማጠናከርና በባንኮችና ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው የገንዘብ አስተላላፊዎች አማካይነት በቂና ቀጣይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መኖሩን ለማረጋገጥ ተግቶ ይሠራል ነው ያለው፡፡

እነዚህ የባንኩ ጥረቶች የሐዋላ ፍሰት ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በሆነ መንገድ አንዲፈጸም ለማድረግና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋትና የልማት ግቦች ለማሳካት የታለሙ ናቸው፡፡

ሕዝቡ ሕጋዊ የውጭ ሐዋላ አገልግሎት አቅራቢዎችን ለይቶ ማወቅ ይችል ዘንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግን ተከትለው በውጭ ምንዛሪ ገበያ አንዲሳተፉ የተፈቀደላቸውን የሐዋላ አስተላለፊ ድርጅቶች ስም ዝርዝር በድረ ገጽ አድራሻ https://nbe.gov.et/mta/ ማግኘት ይችላል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!