አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የኢንዱስትሪ ልማት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ብልጽግና ተደማሪ አቅም ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በደብረ ብርሃን ከተማ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የብራውን ፉድስ የበቆሎ ማቀነባበሪያ እና የምግብና የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
የመደመር መንግሥት በኢንዱስትሪ ልማት ሥራ በመፍጠርና አቅሞችን አሰባስቦ በመጠቀም አስተማማኝና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ያለምነውን የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ ነው ብለዋል።
ግባችን ሥራ መፍጠር፣ ዕድልን ማስፋትና የሕዝባችንን አቅም የሚያንፀባርቅ ኢኮኖሚ መገንባት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በደብረ ብርሃን ያየነው ጅማሮ ከፋብሪካ ማቆም በላይ ለክልሉ የምርታማነትና በራስ መተማመን የአዲስ ዘመን ማሳያ መሠረት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከፍተኛ የመልማት አቅም፣ ለም አፈር እና ስራ ወዳድ ማህበረሰብ ይዘናል በማለት ጠቅሰው÷ የእኛ ኃላፊነት ይህንን አቅም በአርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እና በአመራሩ የተባበረ ክንድ ወደ ተጨባጭ እሴት መለወጥ ይሆናልም ነው ያሉት።
አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት እና የማንሠራራት ዘመን ጉዞ የሰመረ ለማድረግ በሁሉም መስክ ያስመዘገብነውን ስኬት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።
በለይኩን ዓለም